የሩሲያ እና ዩክሬን የሰላም ድርድር በትናትናው እለት በቤላሩስ መካሄድ ጀምሯል፡፡ በቤላሩስ የሚደረገው የሁለቱ አገራት የሰላም ድርድር በዩክሬን የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻን ለማስቆም ያለመ ስለመሆኑ ተመላክቷል፡፡
ብዙ የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሏቸውን የዶኔትስክ እና የሉጋንስክ ግዛቶችን ከጸረ-ሩሲያውያን ለመጠበቅ በሚል ሞስኮ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ዛሬ ሰባተኛ ቀኑን ይዟል፡፡
ከወታደራዊ ዘመቻው ጥቂት ቀናት በኋላ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ÷ አገራቸው ከሩሲያ ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኗን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም የሚደረገው ድርድር በአገራቱ መካከል የተጀመረውን ጦርነት ማስቆም ያስችላል በሚል በተስፋ ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡
አሁን ላይም አገራቱ የሰላም ድርድሩ ከዩክሬን ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ቤላሩስ እያካሄዱ መሆኑን አርቲ ዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንት ፑቲን የአገራቸውን መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሹይጉን ጨምሮ ለከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት፣ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ “ተገቢ ያልሆነ” እርምጃ እና “ሕገ ወጥ ማዕቀብ” መጣላቸውን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ትዕዛዝ ያስተላለፉት የኔቶ አባል አገራት በሩሲያ ላይ “ጠብ አጫሪ መግለጫዎችን” እያወጡ ነው በማለት ሞስኮ ከከሰሰች በኋላ ነው።
ፑቲን አገራቸው የኑክሊየር ጦር መሣሪያን ልትጠቀም እንደምትችል በተዘዋዋሪ ሲናገሩ የቆየ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ንግግር ደግሞ “ማንም ሊያስቆመን ቢሞክር የሚሰጠው ምላሽ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።
አሁን ፕሬዚዳንቱ ለአገራቸው ጦር ሠራዊት የኑክሌር ኃይል ያስተላለፉት የተጠንቀቅ ትዕዛዝ አስገዳጅ ሁኔታ ቢከሰት በፍጥነት እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ነው ተብሏል።
በዩክሬን እና ሩስያ ጦርነት እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች አልቀዋል ፣ በርካታ ንብረት ወድሟል፣ በመቶ ሺዎች ሰላም ፍለጋ ድንበር አቋርጠው ተሰደዋል፣ በሁለቱ አገራት ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚውና በሌላውም ዘርፍ ከፍተኛ ተፅእኖ ተፈጥሯል።
አዲስ ዘመን የካቲት 22 /2014